
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣ ደንብ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣ ደንብ ላይ ውይይት አካሄደ፡፡
======================
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መጋቢት 23/2017ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ከአስራ አንዱም ክፍለ ከተማ ከተወጣጡ የንግዱ ማህበረሰብ ጋር መደበኛ ያልሆነ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ በወጣው ደንብ ቁጥር 184/2017 እና ማንዋል ላይ ውይይት አካሂዷል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ መደበኛ ያልሆነ የንግድ ስርዓት ላይ የተሰማሩትን ወደ መደበኛ የንግድ ስርዓት ለማስገባት ደንብ ቁጥር 184/2017 መውጣቱን ገልፀው ቀጥታ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የንግዱ ማህበረሰብ አካላት ጋር መወያየት ያስፈለገበት ምክንያት ደንቡን አውቃችሁ እንድታስፈፅሙ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጌታሁን አበራ በንግግራቸው የከተማ አስተዳደሩ በርካታ የልማት ስራዎችን እየሰራ በመሆኑ አሁን ካለው የኮሪደር ልማት ስራ ጋር ኢ-መደበኛ ንግድ አብሮ ስለማይሄድ የንግድ ስርዓቱን ለማዘመን ደንብ መውጣቱ አስፈላጊ ነው ብለው ይህን ደንብ በባለቤትነት ወስዳችሁ ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ እንድትሰሩ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ህግ ቡደን አስተባባሪ አቶ መለስ ተገኑ መደበኛ ያልሆነ የጎዳና ላይ ንግድን ስርዓት ለማስያዝ የወጣውን ደንብ ቁጥር 184/2017 እና ማንዋል ሰነድ አቅርበው የወጣውን ደንብና መመሪያ አክብሮ መስራት ከንግዱ ማህበረሰብ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡
ደንቡን ላወጣው ለከተማ አስተዳደሩ ምስጋና ያቀረቡት ተሳታፊዎች በዚህ ልክ ውይይት መደረጉ ጥሩ ነው ፣ የከተማውን ውበትና ፅዳት በጠበቀ መልኩ ደንቡን አክብረን በጋራ እንሰራለን፣ ፈቃዱን ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው የሚሉ ሀሳብና አስተያየቶችን አንስተው በቢሮው ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments